ጋዜጠኛዉ፡- ኦዲት ምንድን ነዉ?
ዋና ኦዲተር፡- ኦዲት ማለት የአንድ ተቋም/ድርጅት የሀሳብ መግለጫዎች ፣የሂሳብ መዛግብት፣ መረጃዎች እንዲሁም የስራ ክንዉኖችን መመርመር፣መገምገምና መተንተን ማለት ነዉ፡፡እነዚህ ግምገማዎችና ትንተናዎችን ማካሄድ ብቻ ሳይሆን የተገኘዉ ዉጤት ትክክለኛነት በማረጋገጥ ለተጠቃሚዉ አካል የኦዲት አስተያየት ማቅረብ ነዉ፡፡
ኦዲት በገለልተኛነት መካሄድ አለበት ካልሆነ ግን ኦዲት ዉጤታማ ሊሆን አይችልም፡፡ ገለልተኛ ማለት ደግሞ ከማንኛዉም ህሊናዊና ቁሳዊ እንዲሁም የውጭ ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ ሁኔታ ኦዲቱን ማካሄድ መቻል አለበት ማለት ነዉ፡፡
ጋዘጤኛ፡- የኦዲት ጥቅሞችን በተመለከተ
ዋና ኦዲተር፡- ኦዲት ብዙ ጥቅሞች አሉት ጥቅሙም ለተለያዩ አካላት ከፍተኛ ጥቅም አለዉ፡፡
አንዱና የመጀመሪያዉ ህብረተሰቡ ነዉ፣ ማንኛዉም ፕሮጀክት ወይም የልማት ስራዎች የሚሰሩት ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ነዉ፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች በሚሰሩበት በጣም በተቀላጠፈ ሁኔታ በጥራትና በጊዜ ተሰርቶ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲዉሉ ግፊት ያደርጋል።
ሌላዉ ለኦዲት ተደራጊዉ ነዉ ኦዲት ተደራጊዉ ስራዉን በሚሰራበት ጊዜ ትክክል ነኝ ብሎ ነዉ የሚሰራዉ ፣ነገር ግን ብዙ ክፍተቶች ሊኖሩት ይችላሉ፣ ብዙ ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡
እነዚህ ክፍተቶችና ስህተቶች ለይቶ በማዉጣት እንዲያስተካክሉ ይጠቅማል ፣አቅጣጫም ያሣያል ማለት ነዉ፡፡ ስለዚህ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት ስራዎቻቸዉን በአግባቡ የሚሰሩ በህጋዊነት መንገድ እንዲሰሩና ዉጤታማ እንዲሆኑ የሚመራ ፣ የሚያግዝና የሚመክር ሙያ ነዉ፡፡
ሌላዉ ለባለድርሻ አካላት በተለይም ለምክርቤት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለዉ፡፡ ምክርቤት እንግዲህ እንደሚታወቀዉ አስፈፃሚ አካላትን ዕቅድ ይገመግማል፣ ያፀድቃል፡፡
የአስፈፃሚ አካላት የልማት ፕሮግራሞችን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ልማት በሚያቅዱበት ጊዜ ወደ ስራ ከመግባታቸዉ በፊት ለም/ቤቱ አቀርበው ያፀድቃሉ፡፡ ይሄንን ዕቅድ ለማሳካት የሚረዳ ወይም የሚያግዝ በጀት ስለሚያስፈልጋቸው ለዚህ የሚሆን በጀት ያዉጃል ማለት ነዉ፡፡
እንግዲህ ዕቅድ ማጽደቅና በጀት ማወጅ የመጨረሻዉ ግብ አይደለም ፡፡ ም/ቤቱ ይሄ የታቀደዉ በጀት በአግባቡ ስራ ላይ መዋሉን ወይም ደግሞ መከናወኑን ማረጋገጥ ይፈልጋል፣ የታወጀዉ በጀት ህግና ስርዓትን ተከትሎ ለዚህ ለዕቅዱ ስራና ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መዋሉን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ ይሄንን ማረጋገጥ ደግሞ የሚችለው ነፃ በሆነ አካል ነዉ። በነፃነት ስራዉን ሰርቶ ይሄንን ነገር አረጋግጦ ለም/ቤት የሚያቀርብ አካል ዋና ኦዲተር ነዉ። ገለልተኛዉ አካል ዋና ኦዲተሩ ነዉ ማለት ነዉ፡፡
ስለዚህ ስለታወጀዉ በጀትና ስለ ፀደቀዉ ዕቅድ አፈጻፀም በተመለከተ፣ ስኬታማነትን በተመለከተ ቅልጥፍናን በተመለከተና የሀብት አጠቃቀም ኢኮኖሚያዊነትን በተመለከተ መረጃን የሚያገኙት ከኦዲት ሪፖርት ነዉ፡፡ የኦዲት ሪፖርትን በመጠቀም አስፈፃሚ አካላትን ከጊዜዉ አንፃር ይገመግማል ማለት ነዉ፡፡
ስለዚህ ኦዲት ለህግ አዉጭዉ አካል ወይም ለም/ቤት ከፍተኛ ግብአት ይሆናል፡፡
ሌላዉ ለፍትህ አካላት በተለይም የመንግስት ሀብትና ንብረት ብክነትን በተመለከተ ከተጠያቂነት ጉዳይ ጋር በተያያዙ ነገሮች ለፍርድ ቤት ፣ ለዐቃቢ ህግ እንዲሁም ለፖሊስ የሚቀርቡ ጉዳዮችን ተጠያቂ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ወይም ሁኔታዉን መርምሮ ለማረጋገጥ የመጀመሪያ የኦዲተር ምስክርነት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ኦዲተር ገለልተኛ ሆኖ የሚሰራ አካል በመሆኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮችን አጣርተዉ ለፍትህ አሰጣጡ እንዲረዳቸዉ ለግብአት የሚያቀርብላቸው ኦዲት ስለሆነ ለፍትህ አካላት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለዉ፡፡
ጋዜጠኛው፡ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ምን ምን እንደተሰራ ቢገልፁልን?
ዋና ኦዲተር ፡- የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተቋመዉ በ1986ዓ.ም ከተማ በክልል ደረጃ ሲቋቋም ክልል 14 የ አዲትና ቁጥጥር መ/ቤት ተብሎ በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ የክልል 14 በዚያን ጊዜ አዲስ አበባ ክልል ነበረችና፣ከዛ በኃላ 2004 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተብሎ ተሰይሞ ተቋቋመ ፣እንደገና 2012 እንዲሁም ስሙን ሳይቀይር ስልጣኑንና ተግባሩን ተጨምሮለት ተሸሽሎ ተቋቋመ ማለት ነዉ ፤የተቋቋመበት ዓላማ በጣም ብዙ ነዉ፡፡
ጥቂቶቹን ለመግለፅ ያህል የመንግስት መ/ቤቶች ፣የልማት ድርጅቶች የፋይናንስ አስተዳደራቸዉ ተገቢዉን የሂሳብ አያያዝ ስርዐት የተከተለ መሆኑን እንድናረጋግጥ ነዉ፡፡እንግዲህ ሂሳብ የራሱ ደረጃ አለዉ ፣የራሱ አሰራር እና መመሪያ አለዉ ፣ይህን የሂሳብ አያያዝ ስርዓትን መከተሉን ማረጋገጥ ነዉ፡፡
ሌላዉ እነዚህ መ/ቤቶች የገቢ አሰባሰባቸዉ የወጪ አፈቃቀዳቸዉ እንዲሁም የንብረት አያያዛቸዉ የተቀመጠዉን ህግና ስርዓት ተከትሎ የተከናወነ መሆኑን በማረጋገጥ የተገኙትን ግድፈቶች እንዲስተካከሉ ሀሳብ መስጠት ነዉ ፡፡ በዚህ ዉስጥ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮች ካሉ ለሚመለከተዉ አካል አቅርቦ አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወሰድ ያደርገዋል ማለት ነዉ፡፡
ቀጥሎ በተለይም ፕሮጀክቶችና የልማት ፕሮግራሞች አሉ እነሱን በቅልጥፍናና በጥራት ተሰርቶ ለተፈለገዉ አላማ በተፈለገዉ ጊዜ መዋላቸዉን ማረጋገጥ፣ያሉትን ክፍተቶች በመጠቆም እንዲስተካከል በማድረግ የተቋቋመ መ/ቤት ነዉ፡፡
እንግዲህ ይሄንን ስራ ከተቋቋመበት ጀምሮ ከሞላ ጎደል እየሰራ ለተጠቃሚዎች ሪፖርት እያቀረበ ቆይቷል። ከዚህም በመነሳት መ/ቤቶች የአሰራር ግድፈቶቻቸዉን አስተካክለዋል። ከዚህ ባለፈ የገንዘብ ጉድለቶች ህግ ወጥ የሆኑ ወጪዎች በብልጫ የሚከፈሉ ወጪዎች በጣም በርካታ ተገኝቷል፡፡
እነዚህን ተከታትሎ ለመንግስት እንዲደርስ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ፡፡ ስለዚህ ኦዲት እነዚህ ዋና ዋና መሰረታዊ የሆኑ አስተዋፅኦ አበርክቷል ማለት ነዉ፡፡
በተቋሙ የግብአት ዕጥረትና ብቃት ያላቸዉ ባለሙያ ዎች አለመኖር ችግርና ሌላ ተግዳሮቶችን በተመለከተ
ዋና ኦዲተር ፡- ኦዲት ተልዕኮዉን ለማሳካት ብዙ ችግሮች አሉበት
አንደኛዉና ዋነኛዉ የባለሙያ ፍልሰት ነዉ፡፡ በኦዲት ሙያ የምያስመርቅ ተቋም የለም የትኛዉም ዩኒቨሲቲ በኦዲት ሙያ የምያስመርቅ የለም፣ በሌሎች ሙያዎች በአካዉንትንግና በአካዉንትንግ ጋር ግኑኝነት ያላቸዉ ባለሙያዎችን ቀጥረን ራሳችን በስልጠና አብቅተን በልምድ አብቅተን ነዉ ኦዲተር የምናደርጋቸዉማለት ነዉ ፡፡ ስለዚህ ኦዲተር በቀላሉ ከገበያ የሚገኝ አይደለም፡፡
ሌላዉ ኦዲት እንግዲህ አሁን የምንሰራዉ በአገር ደረጃም ሆነ በከተማ የምንሰራዉ የኦዲት ስታንዳርድ የጠበቀ ነዉ፣ አለም አቀፋዊ ስታንዳርድ የጠበቀ ነዉ፡፡እኛ የምንጠቀመዉ ማኑዋል ትልልቅ አለማት የሚጠቀመዉ ማኑዋል ነዉ ማለትም በኢንግሊዘኛ (International organization of supreme Audit institution) የሚባለዉ ማኑዋል ነዉ፣አለም አቀፍ ተቋም የሚያዘጋጀዉ ማኑዋል ነዉ የኛ ሀገርም የተቋሙ አባል ናት እንግዲህ በዚህ ማኑዋል የሚያዘጋጀዉ ስታንዳርዶች አሉ ፣ በተለይ የኦዲት ጥራትን በተመለከተ ማለት ነዉ፡፡ ጥራቶች በተለያየ ደረጃ ይከለሳሉ ማለት ነዉ ይሄንን የሚከለሱ አካላት ወይም በባለሙያዎች በመ/ቤቶች ይዋቀራሉ፡፡ ይሄ በየጊዜዉ ደረጃዉን ጠብቆ ካልተሰራ በስተቀር እነዚህ አለም አቀፍ ድርጅቶች የኛን ስራ በየጊዜዉ እየመጡ ይገመግማሉ በዚህ መሰረት እየተሰራ ነዉ ወይ? ምክንያቱም አገራችን ይሄንን አለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርድ እንድንከተል ፈርማለች እንግዲህ ኦዲት አለም አቀፋዊ ማኑዋል ነዉ የምንከተለዉ ብያለሁ፣ በማኑዋል የሚሠራ አይደለም አይሞከርም በቴክኖሎጂ የታገዘ ነዉ፣ሶፍትዌር ነዉ ሶፍትዌር ደግሞ ያለ ላፕቶፕ አይሠራም ፣ ዛሬ 138 የሚሆኑ ኦዲተሮች አሉ ከዛ ዉስጥ 55 ብቻ ነዉ ላፕቶፕ ያላቸዉ፡፡ ስለዚህ ሌሎች ባዶ እጃቸዉን ናቸዉ፣ ስለዚህ ብቁ አይደለንም በዚህ የተነሳ የኦዲት ሽፋናችንም ችግር አለበት ይሄንን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ነዉ ጥረቱን ጀምረናል
ሌላዉ የኦዲት ይደረግልን ጥያቀዎች በጣም ብዙ ናቸዉ በተለይ ከሙስና ማጨበርበር ጋር ከመንግስት ሀብትና ንብረት ብክነት ጋር የተያያዙ በርካታ ጥቆማዎች በመንግስት አካላት ይመጣሉ ፣ከፍትህ አካላት ይመጣሉ፤ ስለዚህ የልዩ ኦዲት ጥያቄ እየበረከቱ መምጣታቸዉ ያንን ሰርተን ማቅረብ ደግሞ ግዴታ አለብን፣ ምክንያቱም የህዝብ አገልጋዮች ነንና እነዚህ ድርጊቶች ህዝባችንን የሚጎዱ ናቸዉና ፣ እኛ ደግሞ ለህግ አካላት ማቅረብ ግዴታ አለብንና እነዚህ ሁሉ ሰርተን ለማቅረብ ቅድም እንዳልኩት ብቁ የባለሙያ ብቃት ያለዉ ባለሙያ እጥረት አለ በብዛትም በጥራትም ማለት ነዉ፡፡ ይሄንን ችግር ለመፍታት የሪፎርም ስራዎች እየሠራን ነዉ ከመንግስት ጋር ሆነን ጉዳዩን ግልጽ አድርገን ተመካክረን ተጋግዘን ቅንጅታዊ በሆነ ሁኔታ ለመፍታት የሪፎርም ስራ ጀምረናል፣ ይሄንን እንፈታለን ብለን እንገምታለን፡፡
ጋዘጠኛዉ፡ ዋና ኦዲተሩ መ/ቤታችሁ እስከአሁን ባለዉ ጊዜያት የተለያዩ የኦዲት ስራዎችን ማከናወን የቻለ ቢሆንም ሰፋ ያለ የኦዲት አገልግሎት ላይ ዉስንነት መኖሩን ይገልፃሉ ምክንያቱን ቢያብራሩልን?
ዋና ኦዲተሩ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ስናየዉ ኦዲት በተፈለገዉ ያህል አድጓል ማለት አይቻልም፣ በእርግጥ በርካታ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ፡፡ብዙ ስራዎችን ሰርተዋል ለከተማዉ፣ ግን መስራት ያለበት ያህል ተሰርተዋል ማለት በጣም አስቸጋሪ ነዉ፡፡ ለምሳሌ በከተማችን በርካታ ኦዲት ተደራጊ የመንግስት ተቋማትና የልማት ድርጅቶች አሉ ፣ የኦዲት ሽፋናችን ምንያህል ነዉ ብለን ብናይ እስከ 2013ዓ.ም ድረስ ከ 12% ያልበለጠ ነዉ ይሄ ከምን የመጣ ነዉ ብለን ስናይ ፣
አንደኛዉ ከሰዉ ሀይል ፣ከባለሙያ እጥረት ነዉ፣ ከፍልሰትም በተነሳ ከገበያ ለማግኘት ያለመቻልም የተነሳ ነዉ
ሁለተኛ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አንፃር፤ እንግዲህ አለም አቀፍ ስታንዳርድ የምንከተል ከሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ከዛዉ አንፃር መሆን አለበት ፡፡
ዛሬ የአፍሪካ አገር እንኳን እነ ታንዛኒያ እነ ኬኒያ ኦንለይን ነዉ ኦዲት ይሄ ደግሞ የሰዉ ሀይልንም በቁጠባ ለመጠቀምና በትንሽ የሰዉ ሀይል ብዙ መስራትና የኦዲት ሽፋንን መጨመር የሚቻልበት ጥሩ ነበረ ቴክኖሎጂ ብንጠቀም ፤ ከዚህ አንፃር በጣም አነስተኛ ነዉ ማለት ይቻላል ፤ አዲስ አበባ ደግሞ የአፍሪካ መዲና ናት የሀገሪቷ ትልቅ ከተማ ናት በትንሹ ለሌሎች ምሳሌ መሆን ነበረበት ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ ከዚህ አንፃር ገና ይቀራል ማለት ነዉ፡፡
ሌላዉ የምናገለግልበት መሳሪያ ኦዲት ነዉ፡፡ ህዝባችን የምናገለግለዉ ኦዲት በማድረግ ነዉ የኦዲት መሳሪያዎች በተለያየ ዕይታ የሚሰሩ መሆን አለባቸዉ ከአንድ አቅጣጫ መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ኦዲት እየተደረገ ያለው የፋይናንሻልና ህጋዊነት ኦዲት፣የልዩ ኦዲትና የክዋኔ ኦዲት ሶስቱ ብቻ ናቸዉ ሌሎች የአከባቢ ኦዲት የለም አከባቢ ኦዲት ማለት ኦዲት እንደ አዲስ አበባ ትልቅ ከተሞች ብዙ ፋብሪካዎች ያሉባት ከተማ ብዙ ብክለቶች የተጋለጠች ከተማ የአከባቢ ኦዲት በማድረግ እነዚህ ከፍተኛ የአከባቢና የጤና ተፅዕኖ የሚያደርሱ የአከባቢ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን መስራት አለብን ፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅድም ያልኩት የአለም አቀፍ ስታንዳርድ ማንዴቱ ሰጥቶናል ማለት ነዉ፡፡ መስራት እንዳለብን ግዴታችን ነዉ የአከባቢ ኦዲት አልተተገበረም፡፡ ሌላዉ ትልቁ የበጀታችን ምንጭ የምንሰበስበው ገቢ ነዉ የምንሰበስበዉ ገቢ ሄዶ በጀት የሚሆነዉ እኛ እንደ መ/ቤት ኦዲታችን ያተኮረዉ በወጭ ላይ ነዉ በጀት ላይ ነዉ ስለዚህ የበጀቱ ምንጭ የሆነዉ የገቢ አሰባሰቢ ገቢ ኦዲት ላይ እስካሁን ስራ አልተጀመረም ማለት ነዉ፡፡ስለዚህ አሁን በሪፎርማችን ይሄንን አካተን ፣ አቅደን በዚህ አመት ከሶስት ወደ አምስት አሳድገን እየሰራን ነዉ የምንገኘዉ ማለት ነዉ፡፡ የአደረጃጀት ችግር አለ በተለይ መሰራት ሲኖራቸዉ ያልተሰሩ ስራዎች አሉ(?)
በጣም ወሳኝ ስራዎች አሉ እነሱ ሁሉ ኦዲት ያለበት ደረጃ የሚያሳይ ገና ማስተካከል የሚጠበቅብን ነው።
ጋዜጠኛዉ፡- በቀጣይ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዋና ኦዲተር መ/ቤት የመጭዉ ጊዜያት የሚያከናዉናቸዉ ስራዎች ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ካሉ ቢገልፁልን?
ዋና ኦዲተር፡- የአመስትና የአስር ዓመት መሪ እቅዳችን አዘጋጅተናል፣ እነዚህ ችግሮቻችንም በዚህ እቅድ ዉስጥ ማቃለል የዕቅዳችን ግብአት አድርገናል፡፡ ከ2013ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2022 ዓ.ም እያንዳንዱ ስትራቴጂዎቻችን ከመነሻ እስከ መድረሻ ምንያህል መስራት እንዳለብን ፤ምን ያህል ማሳደግ እንዳለብን ስራዎቻችን በተለይ የኦዲት ሽፋናችንን ፣ የኦዲት ጥራታችንን፣ ኦዲትን ዉጤታማ ለማድረግ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን እነዚህ ሁሉ ኢስትራቴጂካል አስቀምጠን የኦዲት ሙያዉን ለማሳደግ አቅደናል ቆጥረንም እስከታች እስከ ፈፃሚ ድረስ አዉርደናል፣የመከታተያ ስልታችንን ቀይሰን ለዚህም የ2016 ዓ.ም ወደ ስራ እየገባን ሲሆን ይሄንን በዚህ መሰረት እየሰራን የሚቀጥለዉ ስትራቴጂክ ዘመናችን የኦዲት ሙያዉን ለማሳደግ ያስቀመጥነዉ ነገር አለ ፡፡ በዚህ መሰረት የኦዲት ሽፋናችን ቅድም እንዳልኩት 12% የነበረዉ በቀጣይ አስር ዓመት 100% ለማድረስ ነዉ አቅደን ያለነዉ፡፡ ይህ ማለት እስካሁን ወደ 80 የሚሆኑ መ/ቤቶች ነዉ፡፡ በተለይ ትልልቅ መ/ቤቶች አቶክረን የምንሰራዉ፤ የሚቀጥለዉ እስከ 20 ዓመት ግን ከ 700 ያላነሱ መ/ቤቶች አሉ እነሱን እንሸፍናለን ብለን አስቀምጠናል ማለት ነዉ፡፡ይሄንን ለመሸፈን ግን የሰዉ ሀይልም በየአመቱ በዛ መጠን እየጨመረን ፣በጀቱንም በዛመጠን ፣ሎጂስትኩንም በዛ መጠን፣ የኦዲት ግባቶችንም/መሳሪያዎችንም በዛዉ መጠን በየአመቱ እየጨመረን በ2022 ዓ.ም የከተማዋን ተቋማት በሙሉ በአመት መሸፈን የምንችልበትን ሁኔታ ቀይሰን እየሠራን ነዉ፡፡
እንግዲህ ይህ የእኛ ዓላማ ነዉ፤ይህ የእኛ ራዕይ ነዉ፡፡ ነገር ግን ራዕያችን እንዲሳካ ደግሞ የሚመለከታቸዉ አካላት እገዛ የሚጠይቅ ነዉ፡፡ ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም 95 መ/ቤቶች ናቸዉ በጠቅላላ በሶስቱ የኦዲት ዓይነቶች የተሰሩት ማለት ነዉ፡፡
የፋይናንስና ህጋዊነት ፣ክዋኔና ልዩ ኦዲት አንድ ላይ ተደምሮ 95 መስሪያቤቶች ብቻ ነዉ፡፡በ2014 ግን እነዚህ ወደ 135 ለማሳደግ አቅደን ወደ ስራ እየገባን ነዉ፡፡እነዚህን እያሳደግን በየአመቱ በ2022 መቶ በመቶ ለመሸፈን ነዉ ያቀድነዉ፡፡ ስለዚህ በአንድ አመት ብቻ 42% ዕድገት ማሳየት ማለት ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ያለብንን ችግሮች በዚህ መሰረት እየቀረፈን ሄደን ኦዲቱን እናሳድጋለን፡፡
ሌላዉ ዘንድሮ የጀመርነዉ ከዚህ በፍት የነበሩን ሶስት ዓይነት የኦዲት ብቻ ናቸዉ አሁን ግን ወደ አምስት አሳድገናል ማለት ነዉ፡፡ የኦዲት ጥራት ማሳደግ ደግሞ ገለልተኛ የሆነ የኦዲት ጥራት ማረጋገጫ ቡድን አንድ ቡድን አቋቁመን ፣ ይሄ ኦዲት ስራ ላይ ያልተሰማራ ግን የተሰራ የኦዲት ስራ በሌሎች አካላት የተሰራ ወይም በኦዲተሮች የተሰራ ጥራቱን የሚያረጋግጥ ፣ ይሄ ለኦዲቱ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለዉ፡፡
ሁለተኛ ጥራት ያለዉ ኦዲት ጥራት ያለዉ ግብአት ነዉ ጥራት ያለዉ ግብአት ደግሞ ለዉሳኔ ሰጭዉ አካል ጥራት ያለዉ ዉሳኔ የሚያሰጥ መሆኑ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ፡፡
ሌላዉ ሙያዉን ማዘመን ነዉ ቅድም እንዳልኩት በቴክኖሎጂ መታገዝ አለብን ፤ ከኦዲት ተደራጊ ተቋማት ጋር በቴክኖሎጂ መገናኘት አለብን ፣ በአካል መሄድ ወሳኝ አይደለም፤ ስለዚህ ከአንዳንድ ኦዲት ተደራጊ መ/ቤት በቴክኖሎጂ ግንኙነት ከፈጠርን ኦንላይን ኦዲት መጀመር ያሥፈልጋል በተለይም የተወሰኑ ተቋማት በሁሉም ባንችልም አሁን ባለን ደረጃ በተወሰኑ ተቋማትጋር ግኑኝነት ከፈጠረን ከ 30-40% ጊዜያችን እንቆጥባለን ብለን እንገምታለን፡፡ ለዚህም ለቴክህኖሎጂ የ IT ክፍላችን አደረጃጀት ማሻሻል ነዉ ፣አሁን ራሱ አሻሽለናል፡፡ ከዚህ በፊት በቡድን የነበረዉ ወደ ዳይሬክቶሬት አሳድገን ወደ ስራ እየገባን ነዉ፡፡ይሄ ብቻ አይደለም የኦዲት ስራ ጋር የተገናኘ ኦዲት የሚደግፉ አካላትም የኦፊሰር ስራዎችን ወረቀት አልባ ለማድረግም ስትራቴጂ ነድፈን እየሰራን ነዉ፡፡እነዚህ ሁሉ ኦዲቱን የሚያፋጥኑ ናቸዉ፡፡
ሌሎች የሪፎርም ስራዎች ናቸዉ ሪፎርሙ በጣም ከፍተኛ ሚና አለዉ ብዬ እገምታለሁ
1ኛ አደረጃጀቱን organizational structure የሚቀይር የሰዉ ሀይልም በጥራትና በብዛት ማግኘት የሚያሥችል ይሆናል ፣ ይሄ ከተደረገ እንግዲህ ከሌላዉ ጋር ከተቀናጀን መስራት እንችላለን ብዬ እገምታለሁ
በመጨረሻ ዋና ኦዲተሩ በከተማችን የሚገኙ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት መ/ቤቶች ኦዲት አጠቃላይ ስራዉ ያለዉ ጠቀሜታ በመረዳት ለኦዲት ስራዉ መሳካት ተገቢዉን ሚና እንዲወጡ እንዲሁም ለመንግስትና ለህብረተሰቡ መልዕክቶን ቢያስተላልፉ
ዋና ኦዲተር፡- እኔ የማስተላልፈው መልዕክት
ለኦዲት ተደራጊ ተቋማት ነዉ፡፡ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት የኦዲት ስራ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ቢገነዘቡና ለኦዲቱ መሳካት የራሳቸዉን አስተዋፅኦ ቢያበረክቱ ብዬ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ ኦዲት መ/ቤቶች አሰራራቸዉን እንዲያስተካክሉ የሚረዳ ነዉ፣ ስህተቶቻቸዉን ቶሎ እንዲያርሙ የሚረዳ ነዉ፣ ህጎችን እንዲያከብሩ ነዉ፣ ምክንያቱም አንድ አስፈፃሚ ተልዕኮ ሲሰጠዉ ከሀብት ጋር ነዉ የሚሰጠዉ፣ የሀብት አጠቃቀማችን ደግሞ ህግን የተከተለ ፣ ደንብን የተከተለ መሆን አለበት። ኦዲቱ እነዚህ መፈፀማቸዉን ፣ መከናወናቸዉን አረጋግጦ ወደ ትክክለኛዉ አቅጣጫ የሚመራ ነዉ እንጂ ስህተትን የሚፈልግ ስላልሆነ ይሄንን ተገንዝቦ ለኦዲቱ መሳካት የራሳቸዉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱና የኦዲትን ዉጤት እንዲጠቀሙ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡
ሌላዉ ለመንግስት የማስተላልፈዉ እንግዲህ ትልቁ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሀብት ፍላጎት ነዉ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም ከሀብት ፍላጎት የመነጨ ነዉ የመልካም አስተዳደር ችግር ከሀብት ጋር የተገናኘ ነዉ የሚሰራ ደግሞ ገለልተኛ የሆነ ቡድን ኦዲተር ነዉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ /ለመቀልበስ/ ለማጥፋት ከተፈለገ ለኦዲት ስራ ትኩረት መሰጠት አለበት ይሄ ነዉ የእኔ መልዕክት ፡፡ ተቋማትን ማብዛት አይደለም ፣ለሎች ተቋማትን ማስፋፋት ብቻ አይደለም ለኦዲቱ ዋና የሆነዉ ለመንግስት ሀብት አጠቃቀም ህጋዊነት መሠረት የሆነዉ ኦዲት ነዉና ለኦዲቱ ትኩረት መስጠትና የኦዲት መ/ቤቶችን ቢያጠናክር ቅድም ያልኳቸዉን በማቃለል በኩል ግንባር ቀደም ተባበሪ ቢሆን ጥሩ ነዉ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
ሌላዉ ህብረተሰባችን ነዉ መንግስት በጀት የሚያዉጀዉ ቅድም እንዳልኩት የአስፈፃሚ አካላትን ዕቅድ የሚያፀድቀዉ ለህዝብ ተጠቃሚነት ብሎ ነዉ ፕሮጀክቶች፣ፕሮግራሞችና የልማት ስራዎች ለህዝብ ጥቅም ተብሎ ነዉ የሚሰራዉ እኛ ደግሞ ኦዲት የምናደርገዉ እነዚህን በአግባቡ ተሰርቶ ህዝብን ተጠቃሚ አደርገዋል ወይ? ብለን ነዉ የምንሰራዉ፡፡ ስለዚህ ህዝባችን ከጎናችን መሆን አለበት ማለት ነዉ። በተለይ በዚህ አከባቢ የሚታዩ ግድፈቶችን እያዩ ዝም ማለት የለበትም ማለት ነዉ። ለእኛ መጠቆም ይገባዋል ማለት ነዉ። ምክንያቱም እኛ የቆምነዉ ይሄ ለህዝብ የተመደበዉ ሀብት ለህዝብ ዉሏል ወይስ አልዋለም ብለን ነዉ፡፡
አመሰግናለሁ!!